Psalms 149

የድል መዝሙር

1ሃሌ ሉያ።
አንዳንዶች ከ9 ጭምር እግዚአብሔር ይመስገን ይላሉ።


ለእግዚአብሔር አዲስ ቅኔ ተቀኙ፤
ምስጋናውንም በቅዱሳን ጉባኤ ዘምሩ።

2እስራኤል በፈጣሪው ደስ ይበለው፤
የጽዮንም ልጆች በንጉሣቸው ሐሤት ያድርጉ።
3ስሙን በሽብሸባ ያመስግኑ፤ በከበሮና በመሰንቆ ይዘምሩለት።
4 እግዚአብሔር በሕዝቡ ደስ ይለዋልና፤
የዋሃንንም በማዳኑ ውበት ያጐናጽፋል።
5ቅዱሳን በዚህ ክብር ይጓደዱ፤
በመኝታቸውም ላይ እልል እያሉ ይዘምሩ።

6የአምላክ ውዳሴ በአንደበታቸው፣
ባለ ሁለት ልሳን ሰይፍም በእጃቸው ይሁን፤
7በዚህ ሕዝቦችን ይበቀላሉ፤
ሰዎችንም ይቀጣሉ፤
8ነገሥታታቸውን በሰንሰለት፣
መኳንንታቸውንም በእግር ብረት ያስራሉ፤
9ይህም በእነርሱ ላይ የተጻፈውን ፍርድ ለመፈጸም ነው።
ለቅዱሳኑም ሁሉ ይህች ክብር ናት።

ሃሌ ሉያ።
Copyright information for AmhNASV